ጊፍት ቢዝነስ ግሩፕ በአጣዬ ከተማ ለተጎዱ ዜጎች 3 ሚሊየን ብር የሚገመት የአይነት ድጋፍ አደረገ

በኢትዮጵያ በሪል ስቴት ዘርፍ ላይ ተሰማርቶ በመስራት ላይ የሚገኘው ጊፍት ቢዝነስ ግሩፕ በአጣዬ ከተማ በጦርነቱ ምክንያት ተፈናቅለው በችግር ላይ ለሚገኙ ዜጎች 3 ሚሊየን ብር የሚገመት የአይነት ድጋፍ አደረገ። ድጋፉም የተለያዩ የዕለት ደራሽ ምግቦች፣ ብርድ ልብሶችና ፍራሾችን ያካተተ ሲሆን፤ የጊፍት ቢዝነስ ግሩፕ መስራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ገብረእየሱስ ኢጋታ በከተማዋ ተገኝተው ለተፈናቃዮች እና ለከተማው አስተዳደር አስረክበዋል። ዋና ሥራ አስኪያጁ ድጋፉን ባስረከቡበት ወቅት እንደገለፁት፣ ጊፍት ቢዝነስ ግሩፕ ያደረገው ድጋፍ በዚህ የሚቆም እንዳልሆነ ገልፀው፣ በአሁኑ ወቅት በከተማዋና በኑዋሪዎቿ ላይ የተከሰተው ችግር እጅግ ከፍተኛ እንደመሆኑ በቀጣይም ከተለያዩ አካላት ጋር በመተባበር ድጋፉ ተጠናክሮ የሚቀጥልበት መንገድ እንደሚመቻች ተናግረዋል።

“በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን ከየትኛውም ጊዜ በላይ ለመተባበርና ለመረዳዳት የተነሳሳንበት ወቅት ነው” ያሉት ገብረእየሱስ፣ ይሄ የመተባበር መንፈስ ሳይቀዘቅዝ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የተፈናቃዮችን ችግር በመቅረፍና መልሶ በማቋቋም፣ ተመልሰን ፊታችንን ወደልማት ለማዞር መረባረብ ይገባናል ብለዋል። የአጣዬ ከተማ አስተዳደር ሀላፊ የሆኑት ተመስገን አደፍርስ በበኩላቸው ጊፍት ቢዝነስ ግሩፕ ስላደረገው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበው፤ የአጣዬን ከተማ ጉዳት በሌሎች ከተሞች ከደረሰው ጉዳት ለየት የሚያደርገው በአለፋት 4 ዓመታት ውስጥ በከተማዋ ለ7 ጊዜያት ያህል መሰል ጉዳቶች በመድረሳቸው ነው ብለዋል። በአሁኑ ወቅት የደረሰውም መፈናቀልና ጉዳትም ከተማዋ ከዚህ ቀደም ከደረሰባት ጉዳት ሳታገግም ተጨማሪ ጉዳትን በማስተናዷ የጉዳቱን መጠን ከፍተኛ አድርጎታል ሲሉ ገልፀዋል።

በዚህም ምክንያት በአሁኑ ሰዓት የከተማዋ ማህበረሰብ በተለያዩ ቦታዎች ተፈናቅሎ እንደሚገኝ ያነሱት ተመስገን፣ በቀጣይም ማህበረሰቡን በዘላቂነት መልሶ የማቋቋምና የመደራጀት ሥራም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ በመሆን እየተሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል። የከተማዋ ኮማንድ ፖስትም የከተማዋን ሰላም እና ደህንነት ለማስጠበቅ 24 ሰዓታት እየሰራ እንደሚገኝ የገለፁት ሀላፊው፣ እየተደረጉ ያሉ ድጋፎችን በቅርቡ በተቋቋመው የሎጀስቲክ ኮሚቴ አማካኝነት ፍትሀዊ በሆነ መልኩ ለተጎጂ አካላት እንዲከፉፈሉ እንደሚደረግም አመላክተዋል

Gift Real Estate plc

T: +251 114 67 06 69
E: info@giftrealestate.com.et

______________________________________________

See more

See all news

Compare